የዓለም ፖስታ ቀን ተከበረ

Print
Category: Uncategorised
Published Date Written by Fisseha

የዓለም ፖስታ ህብረት የተመሰረተበት 142ኛ ዓመት በመላው ዓለም በሚገኙ የፖስታ አስተዳደሮች ኦክቶበር 9 ተከብሯል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት “ትውልድ ተሻጋሪ የፖስታ አገልግሎትን በማጠናከር የደምበኞችን ፍላጎት እናረካለን” በሚል መሪ ቃል መስከረም 27 ቀን 2009 ዓ.ም ተከብሯል፡፡
በየዓመቱ ኦክቶበር 9 ተከብሮ የሚውለው የዓለም ፖስታ ቀን ፤ በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት በ19ኙም ዞን ፖስታ ቤቶች በተለይ በዋናው ፖስታ ቤት በአለም አቀፍ የደብዳቤ አጻጻፍ ውድድር ተሳትፈው በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ1ኛ - 3ኛ የወጡ ታዳጊ ወጣቶችን በመሸለም እና በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ውሏል፡፡
በዕለቱ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ሙሌጌታ ቦጋለ ባደረጉት ንግግር ድርጅቱ በመላው ሀገሪቱ 934 ቋሚ የአገልግሎት መስጫ ጣቢያዎች ያሉት እና በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ከመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር በገጠር ቀበሌ ደረጃ ከአስራ አምስት ሺህ በላይ የመረጃ ማዕከላትን በማቋቋም በመረጃ የበለፀገ ህብረተሰብ ለመፍጠር እየሰራ እንደሆነ፤ ባለፈው በጀት ዓመትም 321 የመረጃ ማዕከላት ተከፍተው የፖስታ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡
አቶ ሙሉጌታ አያይዘውም የገጽታ ግንባታን በተመለከተም በተለያዩ ከተሞች ህንጻዎችን በመገንባት ላይ እንደሚገኝና ባለፈው በጀት አመት መጨረሻ ላይም በነቀምት፣ በወሊሶ እና በወልቂጤ ያስገነባቸውን ህንጻዎች የተረከበ ሲሆን በአዲስ አበባም በቱሪስት ሆቴል አካባቢ እያስገነባ ያለውን ህንጻ በዚህ ዓመት ይረከባል ብለዋል፡፡
ድርጅቱ አገልግሎቱን በማዘመን የመልዕክትን ጥራት ለመጨመር እየሰራ ሲሆን በዚህም አመርቂ ውጤት በማምጣት ከአለም ፖስታ ህብረት የአገልግሎት ጥራት የቢ ደረጃ ተሸላሚ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ሰርተፊኬቱንም ቱርክ ኢስታንቡል በተካሄደው የአለም ፖስታ ህብረት 26ኛው ኮንግረንስ ድርጅቱ እንደተቀበለ፣ እንዲሁም በ2018 የህብረቱን ሚኒ ኮንግረንስ ለማዘጋጀት ኢትዮጵያ መመረጧን ከዚህ በተጨማሪም ኢትዮጵያ የካውንስል አፍ አድሚኒስትሬሽን አባልነት መመረጧን ጠቅሰዋል፡፡
የዓለም ፖስታ ህብረት ዋና ፀሐፊ ሚስተር ሁሴን ቢሻር በዓሉን አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት የድንበር የለሽ ግኑኝነት ምሳሌዎች አንዱ የሆነው የአለም ፖስታ ህብረት ይህንን ከግምት በማስገባት ፖስታን ከአንዱ የዓለም ጫፍ እስከ ወደሌላኛው ጫፍ በማደል መተኪያ የሌለው የእርስበርስ ግንኙነት ትስስር ለመፍጠር ከዛሬ 142 ዓመታት በፊት የተቋቋመ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
የደምበኞች ፍላጐት በፍጥነት የሚለዋወጥ መሆኑንና ዘመናዊው የመገናኛና ኢንፎርሜ ሽን ቴክኖሎጂም መል ዕክቱን ደጃፍ ድረስ ማደል ብቻ የማይበ ቃው፣ አገልግሎቱን የት እና መቼ ማግኘት የሚፈልግ አዳዲስ ተጠቃሚ እየፈጠረ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የዓለም ፖስታ ህብረት በኢስታንቡል የዓለም ፖስታ ስትራቴጂ የፖስታው ኢንዱስትሪ ከ2017-2020 እና ከዚያም ባሻገር የሚመራበትን ምቹ የዕቅድ አውታር አዘጋጅቷል፡፡ በዚህ ዕቅድም ስትራቴጂውን ማሣካት የሚያስችል ሶስት ግቦችን ማስቀመጡን ፤ግቦቹም የመሰረተ ልማት ትስስሮሽና የትስስሮሹ ሁለገብ አሰራርን ማጠናከር፣ ዘመናዊ ምርቶች/ አገልግሎቶች ማስፋፋት እና ቀጣይነታቸውን ማረጋገጥ፣ የዘርፉን አገልግሎቶችና ግብይቱን ማስፋፋት መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በዕለቱ በዓለም አቀፍ የደብዳቤ አጻጻፍ ውድድር በሀገር ደረጃ ከ1ኛ-3ኛ ለወጡ ታዳጊ ወጣቶች የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ሙሉጌታ ቦጋለ የተዘጋጀላቸውን የላፕ ቶፕ ፣የ 32 ኢንች እና 24 ኢንች LED ቴሌቪዥን ሽልማት አበርክተዋል፡፡

2011. Custom text here
Joomla 1.7 templates free by Joomla Template Maker and Free Joomla Templates