Home

ፖስታ ዜናዎች

Print
Category: Postal News
Published Date Written by Administrator

 

የፓስፖርት እደላው ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል

ኢዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ከኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳዮች ዋና መምሪያ ጋር በገባው ውል መሰረት በ2009 ግንቦት ወር ላይ በአዲስ አበባ ከተማ የፓስፖርት እደላ ስራ መጀመሩ ይታወሣል፡፡

ድርጅቱ ስራውን በማስፋፋትም ከአዲስ አበባ ከተማው ውጪ ባሉ ከተሞች በባህዳር፣ መቀሌ፣ ድሬዳዋ፣ ሀዋሣ፣ ጅማ፣ ደሴ ስራው እየተሰራ ይገኛል፡፡
በተለይበአዲስ አበባ ከተማ ያለው የፓስፖርት እደላ ደንበኞች በአንድ የአገልግሎት መስጪያ ጣቢያ በብዛት በመገኘታቸው ምክንያት ወደ ቅርንጫፍ ፖ/ቤቶች በማስፋፋት ደንበኞችም አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረጉ ተገቢ መሆኑ ስለታመነበት ስራውን የማስፋት ስራ ቀጥሏል፡፡
በዚህም መሰረት ከዋናው ፖ/ቤት በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ በአራዳ ፖስታ ቤት እና በልደታ ፖስታ ቤት የእደላ አገልግሎት መሰጠት ተጀምሯል፡፡
በአራዳ ፖስታ ቤት የፊደል ተራ A,B,C እና D የሚታደሉ ሲሆን በልደታ ፖስታ ቤት ደግሞ የፊደል ተራ “S” ይታደላል፡፡
የተቀሩት የፊደል ተራዎች በዋናው ፖስታ ቤት እየታደሉ ይገኛሉ፡፡
ደንበኞች በየት አካባቢ ፓስፖርታቸውን እንደሚቀበሉ የኢሚግሬሽን የዜግነት ጉዳዮች ዋና መምሪያ እንዲያስታውቅ የተደረገ ሲሆን የተጀመረው አሰራር ጥሩ ለውጥ እንዳመጣ ተገልጿል፡፡
ድርጅቱ በአሁን ሰዓት በአንድ ቀን ብቻ በዋናው ፖስታ ቤት ከ1450 በላይ፣ በአራዳ ፖ/ቤት ከ640 በላይ በልደታ ፖ/ቤት ከ310 ፓስፖርት በላይ ማደሉን ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ በቀጣይም በተለያዩ አካባቢዎች ከፋፍሎ የማደሉ ስራ እንደሚጐለብት ተገልጿል፡፡
የኢሚግሬሽንና የዜግነት ዋና ጉዳዮች መመሪያ ቢሮውን ወደፊት በጅግጅጋ፣ በአዳማ፣ በጋምቤላ እና በሰመራ ሲከፍት በተጠቀሱት ከተሞች የማደል ስራው የሚጀመር ሲሆን በቅርቡም በአዲስ አበባ ከተማ በተጨማሪነት ድርጅቱ አራት ኪሎ አካባቢ አዲስ ባስገባው ህንፃ ይጀመራል፡፡
በአዲስ አበባ በተለያዩ ቅርንጫፎች የፓስፖርት እደላውን መጀመሩ ደንብኞች ተራ በመጠበቅ ያጠፉት የነበረውን ጊዜ በእጥፉ እንደቀነሰላቸው ከኢ-ኤም-ኤስ የስራ ሂደት የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

የኢ-ኮሜርስ ሥራ ተጀመረ

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ዘመኑ የፈጠረውን መልካም አጋጣሚዎች ወደስራ በመቀየር የአገልግሎት አድማሱን እያሰፋ ይገኛል፡፡
የኢኮሜርስ ገበያ በአለም አቀፍ ደረጃ በስፋት እየተሰራ ቢሆንም በሀገራችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር በዘርፍ በስፋት አልተገባም፡፡
የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት መሰል ስራዎችን ለመስራት አቅሙ እና ልምዱ ያለው ሲሆን፤ በተለይ ደንበኞችን በቅርበት ከማግኘት አንፃር ለኢኮሜርስ ስራው ተመራጭ ያደረገዋል፡፡
ድርጅቱ በራሱ እና ከኢኮሜርስ ካምፓኒዎች ጋር ጥምረት በመፍጠር ስራዎችን የመስራት ዓላማ ይዞ ሲንቀሣቀስ የነበረ ሲሆን በቅርቡም ድንቡሎ ዶትኮም (Dumbulo .com)ከተባለ ሀገር በቀል የኢ-ኮሜርስ ካንፓኒ ጋር እቃዎችን ለተጠቃሚዎች ለማደል ስምምነት ተደርጐ ስራው ተጀምሯል፡፡
በስራው ንግድ ባንክ ክፍያውን በተመለከተ፣ ሸዋ ሱፐርማርኬት እቃዎችን በማቅረብ፣ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ከሸዋ ሱፐርማርኬት እቃዎችን ተቀብሎ በአንድ ቀን ውስጥ ለተጠቃሚዎች ለማድረስ የስራ ድርሻ ወስደዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ወደፊት የራሱን ፕላትፎርም በመቅረጽ ስራውን የመስራት አላማ እንዳለው ከማርኬቲንግ ቢዝነስ ዴቨሎፕመንት የተገኘው ማስረጃ ያሣያል፡፡
በሌላ ዜና የታላቁ ህዳሴ ሩጫ የመወዳደሪያ 250,000 ሁለት/ መቶ ሃምሣ ሺ /ቲሸርት ሽያጭ ለማካሄድ እና ስርጭት ለመስራት ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕ/ጽ/ቤት ጋር ስምምነት ማድረጉ ተገልጿል፡፡

የጥራት ስራ አመራር  (ISO9001:2015)ስልጠና ተሰጠ

የጥራት ስራ አመራር ISO900:2015 ከሚያዚያ 30,2010 - ግንቦት 3,2010 ዓ.ም በድርጅቱ ስብሰባ አዳሪሽ ከኢትዮጵያ ደረጃዎች ኤጀንሲ ከመጡ የስልጠና ባለሙያዎች ሲሆን ከተለያዩ የስራ ሂደቶች የተውጣጡ 30 የሚሆኑ የድርጅቱ ሰራተኞች የስልጠናው ተካፋይ ሆነዋል፡፡
የኢትዮጵያ ፖስተ አገልግሎት ድርጅት የአገልግሎት አሰጣጡን በማሻሻል ጥራቱን የተጠበቀ አገልግሎት ለመስጠትና የጥራት ስራ አመራር ፍልስፍና ተግባራዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑ ታውቋል፡፡
የጥራት ስራ አመራር ስርዓት ISO9001፡2015 ስልጠና አሰራሩን ለመተግበር የሚያስፈልጋቸውን ስታንዳርዶች ግንዛቤ ለመፍጠርና በመቀጠልም በድርጅቱ ተግባራዊ ለማድረግ መሆኑን የፖስታ ጥራትና ደህንነት የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ሃብታሙ በየነ አስታውቋል፡፡
የጥራት ስራ አመራር አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ ስልጠና ከወሰዱ የተቋሙ ሰራተኞች ቅድመ ዝግጅት ስራዎችን የሚያከናውን የትግበራ ግብረ ሃይል (Taskforce) ተቋቁመው ወደ ስራ እንደሚገባም አቶ ሃብታሙ አስረድቷል፡፡
በፖስታ አገልግሎት ዘርፍ አገልግሎቱን የሚሰጡ ዘርፈ ብዙ አለም አቀፋዊና አገር ውስጥ ድርጅቶች እንደአሸን እየፈሉ በመምጣታቸው በጥራት ላይ ያተኮረ የደንበኞችን ፍላጐት የሚያረካ አገልግሎት መስጠት የህልውና ጉዳይ ነው፡፡
ISO9001:2015 ተግባራዊ ሲደረግ ጥራትን መሰረት ያደረገ የስራ አመራር ተግባራዊ ስለሚሆን የተቋሙን የለውጥ ጉዞ አንድ እርምጃ ወደፊት እንደሚያራምድ ታምኖበታል፡፡

የአቻ ለአቻ ስልጠና ተሰጠ

በስርዓተ ፆታ እና በኤች.አይ.ቪ ኤድስ ሜይንስትሪሚንግ የስራ ሂደት የኤች አይቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ቡድን በተለያዩ የስራ ሂደቶችና የስራ ክፍሎች የአቻ ለአቻ ስልጠና ሰጠ፡፡
በተለያዩ የስራ ክፈሎችና በስራ ሂደቶች በመዘዋዋር የአቻ ለአቻ ስልጠና የሚሰጥበት ዋና ዓላማ የድርጅቱ ሰራተኞች እራሳቸውን ከኤች .አይቪ .ኤድስ እንዲጠብቁና ኤች .አይ .ቪ ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚደረገው ርብርብ የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማድረግ መሆኑን የኤች .አይ. ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ቡድን መሪ ሲስተር ረሚላ አህመድ አስታውቋል፡፡
በአቻ ለአቻ ስልጠና ወቅት በዋናነት የኤች አይቪ ኤድስ ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያግዙ ስራዎችና ውይይቶች የሚደረጉ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የኮንዶም ስርጭትና የአጠቃቀም ግንዛቤ መፍጠር አንዱ መሆኑ ታውቋል፡፡
ኤች .አይ.ቪ ኤድስ በደማቸው ውስጥ የሚገኝባቸው ሰራተኞች እራሳቸውን በምን መልክ መጠበቅ እንዳለባቸው እና በአገራችን እንደ አዲስ እየተሰራጨ የሚገኘውን የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ስርጭት ለመግታት ስለሚደረገው ጥንቃቄ በውይይቱ ላይ ይቀርባል፡፡
የኤች.አይ.ቪ ኤድስን በመከላከልና በመቆጣጠር ስርጭቱን ለመግታት ከግንቦት 2 እስከ ግንቦት 4 ቀን 2010 ዓ.ም በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የምርመራና የምክር አገልግሎት በፖስታ አገልግሎት ድርጅት ቅጥር ግቢ ውስጥ መዘጋጀቱንም ሲ/ር ረሚላ አህመድ ገልፀዋል፡፡

2011. Custom text here
Joomla 1.7 templates free by Joomla Template Maker and Free Joomla Templates