Home

Advertisement

we deliver small

ፖስታ ዜናዎች

የሽሬ ፖስታ ህንፃ ግንባታ ተጠናቀቀ

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የአገልግሎት አሰጣጡን ጥራትና ደህንነት በማረጋገጥ የተጠቃሚዎቹን ፍላጐት ለማርካት እየተሰሩ ካሉት ስትራቴጂያዊ ግቦች አንዱ የገጽታ ግንባታ ስራ ነው፡፡
ከነኚህም ዋነኛው ተግባር ያረጁና ለእይታ የማይመቹ የአገልግሎት መስጪያ ጣቢያዎችን በኪራይ፣ በግዢ ወይም በራስ አቅም ህንፃ በመገንባት የተሻለ አገልግሎት መስጠት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በዚሁ መሰረት ድርጅቱ በሽሬ እንደስላሴ ያስገነባውን ባለ 3 ፎቅ ህንፃ ታህሳስ 26 ቀን 2010 ዓ.ም አጠናቅቆርክክብ የፈፀመ መሆኑን የዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ የስራ ሃደት ተ/ቺፍ ኦፊሰር ወ/ት ዘቢደር ታምሩ ገልፀዋል፡፡
ርክክቡን ያከናወኑት የድርጅቱ የድጋፍ ሰጪ ዘርፍ ስራ አስፈፃሚ አቶ ታደለ አሰፋ ሲሆኑ ህንፃው በታቀደለት ጊዜና የጥራት ደረጃ የተከናወነ መሆኑን ገልፀው ግንባታው ለአካባቢው ማህበረሰብ ከሚሰጠው ጥቅም በተጨማሪ ድርጅቱ የደረሰበትን የለውጥ ጉዞ የሚያፋጥን መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የህንፃው ግንባታ በሶስት ዓመት የተጠናቀቀ እና ወጪውም 8.5 ሚሊየን ብር (ስምንት ነጥብ አምስት ሚሊየን) የፈጀ ሲሆን በተመሳሳይም በደብረ ታቦር ከተማ እየተገነባ ያለው ባለ 3 ፎቅ እና በአዲስ አበባ ከተማ አራት ኪሎ በተለምዶ ቱሪስት ሆቴል በሚባለው አካባቢ እየተገነባ ያለው ባለ አራት ፎቅ ህንፃም በቅርቡ ርክክብ ተካሄዶ ወደ ስራ የሚገባ መሆኑን ወ/ሪት ዘቢደር ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ በተለያዩ ከተሞች በተመሣሣይ ከባለ ሶስት እስከ ባለ ሰባት ፎቅ ህንፃዎች ለግንባታ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን ባለፈው ዓመት በአርባምንጭ ባለሁለት ፎቅ፣ በነቀምት፣ በወሊሶ እና በወልቂጤ ከተሞች ባለ ሶስት ፎቆች ህንፃ ግንባታ አከናውኖ በስራ ላይ ማዋሉ ይታወቃል፡፡
እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አራት ሪል እስቴቶች እና ዘጠና ዘጠኝ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ከአዲስ አበባ ውጪም አስራ ሁለት ኮንዶሙኒየም ቤቶች በመግዛት ለህብረተሰቡ በቅርበት አገልግሎት በመስጠት ተደራሽነቱን በማረጋገጥ ላይ ያለ መሆኑ ይታወሳል፡፡

የለውጥ ስራዎች ስልጠና ተሰጠ

በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የሪፎርም ድጋፍና ክትትል የስራ ሂደት ቡድን ለድርጅቱ ሰራተኞች ከታህሳስ 11 እስከ 13/2010 እና ከታህሳስ 16-18/2010 በሁለት ዙር ስልጠና በድርጅቱ ማሰልጠኛ ማዕከል ስለለውጥ ስራዎች ስልጠና የተሰጠ ሲሆን ሁሉም የድርጅቱ ሰራተኞች የስልጠናው ተካፋይ ሆኗል፡፡
በስልጠናው መክፈቻ ላይ የድጋፍ ሰጪ ዘርፍ ስራ አስፈፃሚ አቶ ታደለ አሰፋ እንደተናገሩት በአገራችን ተግባራዊ እየተደረገ የሚኘውን የለውጥ ስራዎችን በሁሉም የመንግስት ተቋማት ወጥ የሆነ አረዳድና አተገባበር ተግባራዊ በማድረግ ወጥ የሆነ ሀገራዊ የአፈፃፀም መለኪያ እንዲኖር በመታሰቡ ለሁሉም የመንግስት ተቋማት የተዘጋጀ ስልጠና በመሆኑ ከዚህ ስልጠና በኋላ ተጨማሪ ክህሎት እና ዕውቀት ይዞ በመውጣት የሚታይ ውጤት ማስመዝገብ ይጠበቅባችኋል ብለዋል፡፡
ስልጠናው በዋናነት የስብሰባ አፈፃፀም መመሪያ፣ የመንግስት ሰራተኞች የስነ - ምግባር ኮድ፣ የውጤት ተኮር ስርዓት፣ የለውጥ ሰራዊት ግንባታ አደረጃጀትና አሰራር፣ የለውጥ መሣሪያዎች ምንነትና ትስስር፣ የህዝብ ክንፍ ተሳትፎና አቅም ግንባታ፣ የዜጐች ቻርተር እና የመልካም አስተዳደር ትግበራ ላይ ያተኮረ መሆኑን የሪፎርም ድጋፍና ክትትል የስራ ሂደት ባለቤት አቶ ትካቦ ረዳ አስታውቀዋል፡፡
ስልጠናውን የሰጡት ቀደም ብሎ የአሰልጣኞች ስልጠና የወሰዱ የድርጅቱ የስራ ኃላፊዎች ሲሆኑ በቀረቡት ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ተካሂዷል፡፡

በኳሊቲ ፈንድ የተገዙ ቫን መኪኖች ወደ ሀገር ውስጥ ገቡ

የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት የአገልግሎት ጥራቱን ለማሻሻል የሚያግዙትን መኪኖች በአለም ፖስታ ህብረት በሚገኝ ድጋፍ ግዢ በማከናወን እርካታ ለመጨመር ጥረት እያደረገ ይገኛል፡፡
ድርጅቱ በኳሊቲ ፈንድ አማካኝነት ጥራቱን ለማሻሻል ለመልዕክት ማጓጓዝ የሚጠቀምበትን አራት ሚኒቫን መኪኖች ተገዝተው ገቢ ሆነዋል፡፡
ያደጉት አገራት ወደ አገራችን የላኳቸው መልዕክቶች ፍጥነታቸው እና ደህንነታቸው ተጠብቆ ለተቀባይ እንዲደርስ በማሰብ የሚሰጡት የአገልግሎት ጥራትን ለማሻሻል የሚሰጥ ፈንድ ሲሆን ድርጅቱ በሚያቀርባቸው ፕሮፖዛል መሰረት መኪኖቹ በአለም ፖስታ ህብረት አማካኝነት እየተገዙ ይላካሉ፡፡ በዚህም መሰረት በተቀረፀው ፕሮጀክት መሰረት ስምንት መካከለኛና ትላልቅ ቫን መኪኖችን ለመግዛት በታቀደው መሰረት አራቱ ሚኒቫኖች ወደሀገር ውስጥ ገብተዋል፡፡ ቀሪዎቹ ትላልቅ ቫኖች ግዢ ላይ ሲሆኑ በጥቂት ወራት ውስጥ ወደሀገር ውስጥ ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዚሁ ፈንድ አማካኝነት ባለፈው አመት ሁለት አውቶብሶች፣ እንዲሁም ባለፉት አመታት ስምንት አውቶቡሶች ሁለት መካከለኛ ቫኖች እና ሌሎች ቁሣቁሶች ተገኝተዋል፡፡
ድርጅቱ መሰል ነገሮችን በማግኘቱ በአገልግሎት ጥራቱ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማሣደር መቻሉ የተገኘው መረጃ ያሣያል፡፡

 የፖስታ ዕውቀትና የሂሳብ ስራ ስልጠና ተሰጠ

103ኛ ዙር መሰረታዊ የፖስታ ዕውቀትና የሂሣብ ስራ ኮርስ ስልጠና የተሰጠው ከጥቅምት 27 እስከ ታህሳስ 26 ቀን 2010 ዓ.ም ለሁለት ወራት ሲሆን ከጅማ እና ከደብረብርሃን ዞን ውጪ ከ17 ዞን ፖ/ቤቶች የተውጣጡ 24 ወንድ እና 25 ሴት በአጠቃላይ 49 የድርጅቱ ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
በስልጠናው ወቅት ስለ ደብዳቤ አሰራር፣ ጥቅል፣ ፋይናንሻል ቢዝነስ፣ ኢ.ኤም.ኤስ፣ የቤት ለቤት ቅበላና ዕደላ፣ የሲምና ቫውቸር ካርድ ማርኬቲንግ አሰራር እንዲሁም የሂሳብ ስራና ሪፖርት አቀራረብ በተመለከተ ሰፋ ያለ ትምህርት እንደተሰጣቸው የትምህርት ክፍል ቡድን መሪ ወ/ሮ አመለወርቅ አብርሃ አስታውቀዋል፡፡
በስልጠናው ወቅት ሰልጣኞች ሰፋ ያለ ውይይት እና ግንዛቤ ለማስጨበጥ ፈተና የወሰዱ ሲሆን በተለያዩ የስራ ክፍሎች በመዘዋወር የተግባር ዕውቀት ቀስመዋል፡፡
ስልጠናው ድርጅቱ የሚያወጣቸውን የለውጥ ዕቅዶች ስራተኞቹ በሚገባ አንዲገነዘቡና በተሰማሩበት የስራ መስክ ለስራው የሚያስፈልገውን ዕውቀትና ክህሎት ታጥቀው ውጤታማ ተግባራትን እንዲያከናውኑ እንደሚያግዝ ታውቋል፡፡
በምረቃው ስነ - ስርዓት ላይ ለሰልጣኞች የምስክር ወረቀት በወ/ሮ ዝናሽ አሰፋ የኢት.ፖ.አ.ድ መሰረታዊ የሰራተኛ ማህበር ሊቀመንበር አማካኝነት ከ1 እስከ 3 ለወጡ ሰልጣኞች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

የብሔር፣ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል ተከበረ

በመላው ሀገሪቱ ለ11ኛ ጊዜ እና በዋናነት በሐረሪ ክልል እየተከበረ ያለው የብ/ብ/ሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን በተመለከተ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ሰራተኞች “ህገመንግስታችን፣ ለዴሞክራሲያዊ አንድነታችንና ለህዳሴ ያችን” በሚል መሪ ቃል በዕለቱ ሐምሌ 29 ቀን 2009 ዓ.ም በድርጅቱ የስብሰባ አዳራሽ በፓናል ውይይት በድምቀት አከበሩ፡፡

     በዕለቱም የድርጅቱ የድጋፍ ሰጪ ዘርፍ ስራ አስፈፃሚ አቶ ታደለ አሰፋ “ህገ መንግስት፣ ብዝሃነትና ዴሞክራሲያዊ አንድነት” በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን ሰነድ ለፓናል ውይይት አቅርበዋል፡፡ 

     በውይይቱም የኢ.ፌዲሪ ህገ መንግስት ዋና ዋና ባህሪያትን፣ ህገ መንግስትና ብዝሃነት፣ የብዝሃነት ጥያቄዎችና አያያዛቸው፣ ስኬቶች፣ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስመልክቶ በቀረበው ሰነድ ላይ በስፋት ውይይት ተካሄዶባቸዋል፡፡

    በበዓሉም የሻማ ማብራትና የዳቦ ቆረሳ ስነ-ስርዓት በአቶ ታደለ አሰፋ እና በመሰረታዊ ሰራተኞች ማህበር ሊቀመንበር ወ/ሮ ዝናሽ አሰፋ የተከናወነ ሲሆን የጥያቄና መልስ ውድድር ስነስርአት ተካሂዶ ለተወዳዳሪዎችም ሽልማት ተበርክቷል፡፡  

2011. Custom text here
Joomla 1.7 templates free by Joomla Template Maker and Free Joomla Templates